የእንስሳት ኢንቨስመንት ግብይት ስትራቴጂን ለማርቀቅ እንዲሁም የእንስሳትና እንስሳት ውጤት ግብይት ረቂቅ አዋጅን ማዳበር የሚያስችል ውይይት እየተደረገ ነው፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሳ ኢንቨስትመንትና ምርት ግብይት ዴስክ ኃላፊ አቶ ከድር ሉባንጎ መንግስት ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችን እና መመሪያዎችን በመቅረፅ ከእንስሳት ሀብቱ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የእንስሳትና እንስሳት ውጤት ግብይት ረቂቅ ስትራቴጂን እና አዋጅን ለአብነት የጠቀሱት ዴስክ ኃላፊው፣ ረቂቆቹ ፀድቀው ወደ ትግበራ ሲገቡ በእንስሳትና የእንስሳት ውጤት ግብይት ሂደት የምርት ጥራትን የሚያጓድሉ አሰራሮችን ያስቀራሉ ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከ70 ሚሊየን በላይ የዳልጋ ከብት ያላት ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ጥቅም አላገኘችም፡፡
የመኖ አቅርቦት እጥረትና የዋጋ ንረት፣ የሀገር በቀል ዝሪያዎች ምርታማነታቸው አነስተኛ መሆን እንዲሁም በቂ የእንስሳት ጤና አገልግሎት ተደራሽ አለመሆን እንደ ተግዳሮት ይጠቀሳሉ፡፡